ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ኦቲዝም ሶሳይቲ ምስረታ መድረክ በኢሊሌ ሆቴል የተካሄደ ሲሆን ለረጅም ዘመናት ስንሻው የቆዬው ሁሉንም በኦቲዝም ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች እና ማህበራት፣ ባለሙያዎች እና ቤተሰቦች እንዲሁም በጉዳዩ ፍላጎት ያላቸውን ባለድርሻ አካላት የሚያቅፍ ሀገር አቀፍ የኦቲዝም ሶሳይቲ ምስረታ እዉን ሆኗል።
በዚህ መድረክ ላይ ታሪኩን ያጋራው ወጣት ዳንኤል ኤፍሬም በኒያ ፋዉንዴሸን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል ዉስጥ ለ3 ዓመታት የኦቲዝም ክትትል እና ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን ለዉጥ በማምጣት ዛሬ በሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመማር ላይ ይገኛል። በጉባኤው ላይ ያቀረበው አስቀናቂ ንግግር እና የህይወት ጉዞ ምስክርነት እነሆ!

የተከበራችሁ የኢፌዲሪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች፣ የተከበራችሁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የክልል ክልል ማስተዳድር ተወካዮች፣ ተጋባዝ እንግዶች፣ የኦቲዝም መዕከል መሪዎችና ሠራተኞች፣ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ውድ ወገኖቼ እና ቤተሰባቸው በዚህ ታሪካዊ ቀን በዚህ የተሰበሰባችሁ ታዳሚያን ሁሉ፤ የእግዚአብሔር ሠላም ይብዛላችሁ፡፡
እኔ ዳንኤል ኤፍሬም እባላለሁ፤ ሃያ አንድ ዓመቴ ሲሆን የጆይ ሴንቴር የኦቲዝም መዕከል የቀድሞ ተማሪ ነኝ፡፡ ከ2002 እስከ 2003 ዓ.ም. የጆይ የኦቲዝም መዕከል ስረዳ ቆይቻለሁ፡፡ በቆይታዬ በተወደደችው በወ/ሮ ዜሚ የኑስ እና በማዕከሉ ድንቅ ሠራተኞች በተደረገልኝ ሙያዊ እገዛ፣ በወላጆቼ ጸሎት እና በእግዚአብሔር ልዩ ቸርነት ከኦቲዝም ችግር ወጥቼ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ገብቼ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቴን በድል ጨርሻለሁ፤ ለዩኒቨርስቲ መግቢያ የሚሰጠውን ፈተና በእግዚአብሔር እርዳታ አልፌ ዛሬ በዩኒቨርስቲ የኮምፕዩቴር ሳይንስ የ1ኛ ዓመት ተማሪ ነኝ፡፡ ለዚህ ለመብቃቴ ትልቅ ድጋፍ ለሰጡኝ ለወ/ሮ ዜሚ የኑስ እና ለጆይ ኦቲዝም መዕከል ሠራተኞች ልባዊ ምስጋዬን አቀርባለሁ፡፡
በዚህ አጭር ምስክርነቴ የነበረኩበትን ከባድ ችግር፣ ቤተሰቤ በችግሬ ምክንያት የከፈለውን ታላቅ መስዋዕትነት እና በተለይም ጆይ ሴንቴር የኦቲዝም መዕከል ያደረገልኝ ሙያዊ እገዛ እና የፍቅር ሥራ በሕይወቴ የመጣውን ታላቅ ለውጥ ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡
ወላጆቼ እንደነገሩኝ የኦቲዝም ችግር የገጠመኝ በሁለት ዓመት ከአራት ወር አከባቢ ነበር፡፡ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት እንደ ማንኛውም ጤነኛ ልጅ በደስታ እጫወት ነበር፤ ከወላጆቼ ጋር አወራ እና እግባባ ነበር፤ ራሴን ችዬ እመገብ እና እልብስ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ልጅ ስለነበርኩ ለቤተሰቤ የዓይን ማረፍያና ደስታ ነበርኩ፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ድንገት በማልረዳው ችግር ውስጥ ገበሁ፤ የኦቲዝም ችግር ከገጠመኝ በኋላ በዕለታዊ ሕይወቴ እየሆኑ የነበሩትን አሳቀቂ ነገሮች፣ በራሴ ላይ አደርግ የነበረው ጎጂ ነገሮች እና ለወላጆቼ ልብ የመጣውን ሐዘንና መከራ እኔ አልረዳውም ነበር፤ ነገር ግን ወላጆቼ ከኦቲዝም ካገገምኩ በኋላ የነገሩኝ በአጭሩ አካፍላለሁ፡፡
ወላጆቼ እንደ ነገሩኝ የኦቲዝም ችግር እንደተከሰተ በድንገት ባህርዬ ተለዋወጠ፤ ደስታዬ ጠፋ፤ ሐዘንተኛ ሆንኩ፤ መናገር አቆምኩ፤ ወላጆቼን በዓይን መየት አቆምኩ፤ ምክንያቱ በማተወቅ ሁኔታ ለብዙ ሰዓታት አለቅስ ነበር፤ ወላጆቼ እንደነገሩኝ ራሴን የሚጎዱ ብዙ ነገሮችን አደርግ ነበር፤
ወላጆቼ የተለያዩ የጤና ባለሙያ እንዲመረምሩኝ አድርገው ነበር፤ ነገር ግን በወቅዱ ስለ ኦቲዝም ብዙ ግንዛቤ ስላልነበረ በዚህ ችግር እየተሰቃየሁ መሆነን ለሁለት ዓመታት ያወቀልኝ ሐኪም አልነበረም፤ ወላጆቼ ለሴኮንድ እንኳን ብቻዬን ሊተውኝ አይችሉም ነበር፤ በተለይ ሌሊት ለብዙ ሰዓታት አለቅስ ስለነበረ እናቴ እኔን ለመንከባከብ ብላ እንቅልፍ አልባ ሌሊት ታሳልፍ ነበር፤ በዚህ አጋጣሚ እናቴን ማመስገን እፍልጋለሁ፡፡
ዛሬም በኦቲዝም ችግር ውስጥ ያሉት ህፃናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች በብዙ ችግሮች እንደሚሰቃዩ እረዳለሁ፤ ልቤ እጅግ ያዝንላቸዋል፤ በዚህ የተገኛችሁ የመንግሥት አካላት ይህንን በልባችሁ እንድትይዙ አደራ እላለሁ፡፡ በኦቲዝም ችግር ውስጥ መሆነ የታወቀው ከወላጆቼ ጋር ወደ ሲንጋፖር በሄድኩበት ወቅት በተደረገልን ምርመራ ነበር፤ ከዚያ እንደተመለስን ወላጆቼ ወደ ጆይ ኦቲዝም መዕከል ወሰዱኝ፤ ውድ እናታችን ዜሚ ዬኑስ ችግሬን አይታ እጅግ አዘነችልኝ፤ በአስቸኳይ ወደ መዕከሉ ገብቼ ሙያዊ እገዛ እንዳገኝ ወሰነች፤ ለዚህም መልካም ሥራዋ መታሰቢያዋ የተባረከ ይሁን፡፡
በጆይ ኦቲዝም መዕከል በነበርኩበት ሁለት ዓመታት ተዓምራዊ ለውጥ በሕይወቴ ተከሰተ፤ በየዕለቱ በሚደረግልኝ ሙያዊ እገዛ ቀስ በቀስ ቃላትን ማውጣት ቻልኩ፤ ከዚያም አጭር ዐረፍተ ነገሮችን መናገር ጀመርኩ፤ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ አስቸጋሪ ባህርያቴ ተለወጠ፤ ራሴን መመገብና ማልበስ ቻልኩ፤ ራሴን ችዬ መጸዳዳት እና የግል ንጽህናዬን መጠበቅ ቻልኩ፤ በመጨረሻም መፃፍ እና መንባብን አስተማሩኝ፡፡
በእነዚያ ወሳኝ ሁለት ዓመታት በጆይ ኦቲዝም መዕከል በተደረገልኝ ሙያዊ እገዛ እና እንክብካቤ ሕይወቴ ተለወጠ፤ ወላጆቼ እረት አገኙ፤ እኔም የተለመደ ኑሮ መኖር እና ትምህርቴን እንደ ሌሎች ልጆች ተምሬ ለነገ ሕይወቴ ራሴን እያዘጋጀሁ እገኛለሁ፡፡ በሀገራችን ያሉት ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩት ልጆች ሁሉ እኔ በጆይ የኦቲዝም መዕከል ያገኘሁትን ዓይነት ሙያዊ እገዛ ቢያገኙ በሕይወታቸው ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ እና እኔ የደረሰኩበት ቦታ ሊደርሱ እንደሚችሀሉ አምናለሁ፡፡
ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የኦቲዝም ማዕከላትን በማስፋፋትና ያሉትንም በበቂ ሁኔታ በመደገፍ የእነዚህን ድንቅ ልጆች ሕይወት የመቀየር ዘላቂ ሥራ እንድትሠሩ አደራ እላለሁ፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መብት የሆነውን የትምህርት ዕድል፣ የጤና እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩት ልጆች ተደራሽ በማድረግ ራሳቸውን የሚችሉ አምራች ዜጎች እንድታደርጉአቸው በእግዚአብሔር ስም በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡













