ህዳር 23 / 2018 ኒያ ፋውንዴሽን /ጆይ ኦቲዝም ማዕከል/ ለኦትስቲክ ልጆች እናቶች አቅም ግንባታ የመነሻ የሚሆን ካፒታል በዛሬው እለት ርክክብ ተደረገ።
ፕሮጀክቱ በቡታጅራ ከተማ ዘላቂ እና ዉጤታማ እንዲሆን የሰለጠኑ 6 እናቶችን በማህበር በማደራጀት ስራ ለማስጀመር አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን የማጠናቀቅ ስራ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ስልጠናውን ያጠናቀቁ እናቶች “አድል የበግ ማደለቢያ” እና “ቴገም የበግ ማደለቢያ” በሚባሉ ሁለት ማህበራት ተደራጅተው የንግድ ፈቃድ፣ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር እንዲሁም የንግድ ስራ ዕቅድ (ቢዝነስ ፕላን) በማጠናቀቅ ለኒያ ፋዉንዴሽን ጋር የውል ስምምነት አድርገዋል።
በርክክቡ ወቅት ንግግር ያደረጉት የምስራቅ ጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጉግሳ ኦቲዝም በቤተሰብ ፣ ብሎም በእናቶች ላይ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ፣ የአመለካከት ግድፈቶቶችን ለማስተካከልና ለውጤታማ ለገቢ ማስገኛና የሥራ ዕድል ፈጠራ የእናቶችን አቅም መገንባት ላይ ድርጅቱ በመስራቱ ይበልጥ ለስራ የሚያነሳሳ መሆኑ ገልፀዋል።
የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ጥላሁን ለኦትስቲክ ልጆች እናቶች በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሴቶችን በኢኮኖሚ አቅም የማጎልበት ስራዎችን በዉጤታማነት ድርጅቱ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚበረታታ በመሆኑን እኛም ከጎናቸው ሆነን እናግዛለን ብለዋል።



ኦቲዝም ተጠቂ ልጆች እናቶችን በመደገፍና በማብቃት ዉጤታማ ዜጋ እንዲሆኑ የማስቻል በመሆኑ ይህንን ህልም እውን ለማድረግ ጭምር በርትተን በመስራት ልናገዛቸው እንደሚገባማ አብራርተዋል።
ኒያ ፋውንዴሽን /ጆይ ኦቲዝም ማዕከል/ ስራ አሰኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ እሌኒ ዳምጠው በ2025 ከጊዳቦ ፖለሲ ማዕከል ባገኘነው የገንዘብ ድጋፍ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡታጅራን ጨምሮ በአራት ክልሎች ተግባራዊ በማድረግ ላይ በምንገኘው ለኦቲዝም ተጋላጭ የሆኑ ልጆች ያሏቸው እናቶችን ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም የማጎልበት ስራ ላይ እናቶችን በገቢ ማስገኛ ስራዎች ዙሪያ በማሰልጠን እና የመነሻ መስሪያ ካፒታል በማመቻቸት ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ዓላማን ሰንቀን በቡታጅራ እየሰራን ያለው ስራ ለውጤታማነቱ አብረን መስራት ይገባናል ብለዋል።











